ትናንት ምሽት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት መርሀግብር መቋጫ ግጥሚያ ዲን ኮርት ላይ በዋትፎርድ እና አርሰናል መካከል ተካሂዶ መድፈኞቹ 1 ለ 0 በሆነ ጠባብ ውጤት በመርታት ደረጃቸውን አሻሽለዋል፡፡
በምሽቱ ጨዋታ አርሰናች አሸናፊ የሆኑበትን ብቸኛ ግብ የባለሜዳዎቹ ግብ ጠባቂ ቤን ፎስተር የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ጋቦናዊው ፔር ኤምሪክ ኦባማያንግ አስቆጥሯል፡፡
ከግቧ መቆጠር አንድ ደቂቃ በኋላ የዋትፎርድ አምበል ትሮይ ደኒ በአርሰናሉ ሉካስ ቶሬራ ላይ በሰራው ጥፋት በዕለቱ አርቢትር ክሬግ ፓውሰን ቀጥታ ቀይ ካርድ ተመልክቷል፡፡
በ10 ተጫዋቾች 80 ደቂቃዎችን የተጨወቱት ባለሜዳዎቹ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል፡፡
መድፈኞቹም ቢሆኑ ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥረው ማሸነፍ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች አልተጠቀሙባቸውም፡፡
ድሉን ተከትሎ አርሰናል ከቼልሲ ዕኩል 66 ነጥቦችን በመያዝ በግብ ክፍያ በልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በፕሪምየር ሊጉ ከዋንጫው አሸናፊ ፉክክር ዕኩል በሚቀጥለው የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት የሚደረገው ትግል አጓጊ ነው፡፡