ዛሬ ምሽት ቀሪዎቹ የቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ቡድኖች ይለያሉ
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ግጥሚያዎች ዛሬ ምሽትም ቀጥለው ይካሄዳሉ፡፡
በአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ የሚመራው ሊቨርፑል ወደ ፖርቱጋል አምርቶ እስታዲዮ ዶ ድራጋኦ ላይ ከፖርቶ ጋር ምሽት 4፡00 ሲል ይፋለማል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር አንፊልድ ላይ ተገናኝተው፤ በቀያዮቹ 2 ለ 0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን በዛሬው ምሽት የመልስ ፍልሚያ የፖርቱጋሉ ቡድን በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ወደ ቀጣዩ ዙር ለመሸጋገር ከ2 ለ 0 ባለፈ የግብ መጠን ማሸነፍ ይኖርበታል፡፡
በሊቨርፑል በኩል ተከላካዩ ደያን ሎቭረን እና ኦክስሌድ ቻምበርሊን ፖርቶን ከሚገጥመው ቡድን ውስጥ ያልተካተቱ ሲሆን ጆ ጎሜዝ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል፡፡
በፖርቱ ደግሞ ተከላካዩ ፔፔ እና ሄክቶር ሄሬራ ከቅጣት ተመልሰው ቡድናቸውን በምሽቱ ያገለግላሉ፡፡
ቀያዮቹ ግማሽ ፍፃሜውን የሚቀላቀሉ ከሆነ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ይሆናል፡፡
ሌላኛው በተመሳሳይ ሰዓት የሚደረገው ግጥሚያ ደግሞ እንግሊዝ ምድር ላይ ሲከወን ማንችስተር ሲቲ በኢቲሃድ ቶተንሃም ሆትስፐርን ይገጥማል፡፡
በአዲሱ ሜዳቸው የ1 ለ 0 ድል ያስመዘገቡት ስፐርሶች ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት እና ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በምሽቱ ከፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል፡፡
የቻምፒዮንስ ሊግ ልምድ ያለው ፔፕ ይሄንን ጨዋታ በተሻለ ውጤት አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን ሊዋሀድ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በጨዋታው ሀሪ ኬን ፣ ኢሪክ ዳዬር ፣ ሰርጂ ኡርዬ እና ሃሪ ዊንክስ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን ደል አሊ እና ኢሪክ ላሜላ የመሰለፍ ጉዳይ እየታዬ እንደሆነ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ አስታውቀዋል፡፡
በሲቲ በኩል አማካዩ ፈርናንዲንሆ እና አጥቂው ሰርጂዮ አጉዬሮ ለግጥሚያው ብቁ መሆናቸው ሲነገር ኦሌክሳንድር ዚንቼንኮ ግን አጠራጣሪ ነው ተብሏል፡፡