የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ከመጋቢት እስከ መጋቢት የተሠሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን የሚገመግም የሁለት ቀን የምሁራን አውደ ጥናት እያካሄደ ነዉ፡፡
አውደ ጥናቱ የአንድ ዓመቱን ሂደት በምሁራዊ እይታ ለመዳሰስ፣ ለመገምገምና ለመመርመር ያለመ ነው፡፡
30 ምእራፎችን በሚያካትተው የጥናት መጽሐፍ ላይ የሚወጡ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የሚገመገሙበት የሁለት ቀን የምሁራን ውይይት ከሚያዝያ 11 ቀን 2011 ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ ጥናት ያካሄዱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ምሁራን እየተሳተፉበት ነዉ፡፡
ይህ የጥናት መጽሐፍ የፖለቲካ ለውጥና ተሐድሶ፣ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለውጥ፣ ሀገረ ብሔር/ሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ የውጭ ግንኙነትና የሀገር ደህንነት የሚሉ አራት አንኳር ርእሰ ጉዳዮችን የሚዳስስ ይሆናል ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እንደገለጸዉ የመንግሥት ተወካዮች የአስተዳደሩን አቅጣጫና የውይይት አውድ በመጀመርያ ለተወያዮች የተዋወቀ ሲሆን ፤በጠ/ሚር ጽ/ቤት ሚኒስትር ድኤታ ፍስሥሐ ይታገሡ በፖለቲካ ማሻሻያ ዙሪያ በለውጡ ስፋትና ወሰን ላይ የተገኙ ስኬቶችን በማሳደግ፣ ስህተቶችን በማረም የመጪውን ትውልድ ፍላጎትና ተስፋ በማስጠበቅ ላይ አተኩረዉ ቀዳሚዉን ንግግር አድርገዋል።
ምክትል ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ በበኩላቸዉ ሕግን ከመለወጥና ከማሻሻል፣ መዋቅራዊ አሠራርንና አዲስ አመራር መሾምን በተመለከተ የመንግሥትን ቁርጠኝነት አንሥተዋል።
በተቋማት ግንባታና የሕግ ማዕቀፎችን መሠረት በመጣል አካታችና ተወዳዳሪ የፖለቲካ ከባቢ ከመፍጠርና የሕግ አሠራርን ከማዘመን አንፃርም የተሠሩትን ሥራዎችም ለዉይይት የቀረቡ ሀሳቦች ናቸዉ፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የቃኙት የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች አንሥተዋል፡፡ ዘላቂ፣ መጠነ ሰፊና ገበያ ተኮር ዕድገትን ጠቅሰዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም ለቀጣናዊ የንግድ ውሕደትና የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ባለሀብቶችን ለማሳተፍ ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ በውጭ ግንኙነት ዙሪያ የመጡ የለውጥ ሂደቶችን ያብራሩ ሲሆን ፤የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጣዊ አሠራር ማሻሻያን በተመለከተ በተለይም የሀገር ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴው እንደምን የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት እንዳሳደገና እንደለወጠ ገልጸዋል።