የእምቦጭ አረምን ጨምሮ ከቆሻሻ ነዳጅ ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የኢትዮጵያውያን የፈጠራ ስራዎችን ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ የሚገኘው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአቶ አበሻ ዳጌ የፈጠራ ስራ የሆነውን ከቆሻሻ ነዳጅ የማምረት ፕሮጀክትን ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ ነው፡፡
የፈጠራ ስራው እምቦጭ ና የፕላስቲክ ቆሻሻን ጨምሮ ከማንኛውም ቆሻሻ ውጋጅ ነጭ ጋዝ፣ ቤንዚን፣ ኬሮሲን፣ የአውሮፕላን ነዳጅና ሚቴን ማምረት የሚያስችል ነው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ከሚገኘው ተረፈ ምርት ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ፤ ግሪስ፤ ሻማ፣ የጫማ ቀለምና ሌሎችንም መስራት የሚያችል የፈጠራ ስራ ነው፡፡
የነዳጅ ምርቱን በፍጥነት ለመጀመር ለነዳጅ ማምረት ሂደት የሚጠቅም ያልተወሳሰበ ማሽን ለመስራት የሚችል የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሙ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ከኬሚካና ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጠው ይህ ቡድን ለነዳጅ ማምረቻ የሚያገለግል የማሽን ዲዛይን ሰርቶ ካቀረበ በኋላ ወደ ማሽን ምርት ተገብቶ በየከተሞቹ ነዳጅ ማምረት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ይሰራል፡፡
ምርቱ ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ በዘርፉ የተሻለ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በማሳተፍ ይሰራል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታው ጀማል በከር ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ ለማስቀረትና ለመንግስት ፈተና የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት ይሰራል ብለዋል፡፡
አቶ አባሻ ዳርጌ ይህንን ምርምር ከ10 አመት በፊት ጀምሮ ሲሰሩ እንደቆዩና በተለያዩ የመንግስት አካላት ጫና ወደ ስራ ማስገባት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
የፈጠራ ባለሙያው የካርበን ልቀትን እስከ 95 በመቶ መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የእንቦጭ አረምን አንድም ወደ ነዳጅነት መቀየር አንድም ደግሞ ብዝሃ ህይወቱ ሳይጎዳ እዚያው ባለበት ለማጥፋት የሚያስችል የፈጠራ ስራም አለኝ ብለዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒቴር የስራ ሃላፊዎች ከዚህ ቀደም ቆሻሻን ወደ ነዳጅ የሚፈተርበትን ሂደት በቦታው ተግኝተው መመልከታቸዉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡