በኡጋንዳ ከፍተኛ የኢቦላ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተገለፀ፡፡
የኢቦላ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰባት ኮንጎ ህገወጥ ስደተኞች ወደ ሀገሪቱ እየፈለሱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው የቫይረሱ ስርጭት ስጋት የሆነው፡፡
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከወራት በፊት በተቀሰቀሰው ግጭት የተነሳ ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡
ከተፈናቃዮቹ ጥቂቶቹ በኡጋንዳ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ወደ ድንበር ከመድረሳቸው በፊት በወታደሮች ተይዘው የኢቦላ ቫይረስ ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የኡጋንዳ መንግስት ምንጊዜም ስደተኞችን ለመቀበል በራችን ክፍት ነው ያለ ሲሆን፤ አሁንም ስደተኞችን መቀበላችንን እንቀጥላለን ፤ነገርግን የሀገራችንን ዜጎች ጤና ስጋት ላይ የሚጥል እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንወስዳለን ብሏል፡፡
ጥቂት የማይባሉ ተፈናቃዮች በህገ ወጥ መንገድ የኡጋንዳን ድንበር ጥሰው እየገቡ በመሆኑ የቫይረስ ስርጭት ይከሰታል የሚለው ስጋት እያየለ መጥቷል፡፡
ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ጉዳዩ እንዳሳሰባቸውና ለስደተኞቹ አስፈላጊውን ህክምናና እርዳታ ለማቅረብ መቸገራቸውን የገለጹ ሲሆን ጾታዊ ጥቃቶች ሊከሰቱ ይችላል የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኮንጎ የኢቦላ ቫይረስ ከተቀሰቀሰበት ከፈረንጆቹ 2018 አንስቶ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን ከ9መቶ በላይ የሚሆኑ መሞታቸው ይታወሳል፡፡
.