ከ15 ዓመታት በፊት በ2004 የተጀመረው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በ16ኛ ዙር ውድደሩ ፍፃሜ ላይ ይገኛል፡፡
የ2018/19 የቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታ ባለፈው ሳምንት የተከናወነ ሲሆን የመልስ ፍልሚያው ደግሞ በመጪው ዕሁድ ግብፅ አሌክሳንድሪያ ላይ በግብፁ ቡድን ዛማሊክ እና በሞሮኮው ሬኔይሳንስ ስፖርቲቭ ዴ ቤርካኔ መካከል ቦርጅ አል አረብ ስታዲየም ላይ ይደረጋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት ዕሁድ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ሞሮኮ ላይ አድርገው የነበረ ሲሆን ቤርካኔ ባለቀ የጭማሪ ሰዓት በቶጓዊው ተጫዋች ኮድጆ ፎ -ዶህ- ላባ ብቸኛ ጎል 1 ለ 0 ድል ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ለ16 ዓመታት ያህል ያለባቸውን የአህጉራዊ ዋንጫ ድርቅ ዘንድሮ ለመግታት እየጣሩ የሚገኙት ዛማሊኮች፤ የመጀመሪያ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫቸውን ከፍ ለማድረግ፤ በሜዳቸው እና ደጋፊያቸው ፊት የሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ላይ ቢያንስ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ግድ ይላቸዋል ፡፡
ዛማሊክ ከዚህ ቀደም 5 የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ 3 የካፍ ሱፐር ካፕ ወይንም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በአፍሪካ መድረክ አሳክቷል፡፡ ነጭጭ ጀብደኞች በኮንፌሬሽን ዋንጫ ታሪክ ለፍፃሜ ሲበቁ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በውድድሩ ከዚህ በፊት ያላቸው ትልቅ ስኬት 2015 ያሳኩት የግማሽ ፍፃሜ ዙር ላይ መድረስ ነበር፡፡
ዛማሊክ ለመጨረሻ ጊዜ የተቀዳጀው ዋንጫ የካፍ ሱፐር ካፕ ሲሆን በ2003 ካይሮ ላይ የሞሮኮውን ዋይዳድ ካዛብላንካ በመርታት ነው፡፡
በቅፅል ስማቸው ዘ ኦሬንጅ ሲቲ ተብለው የሚጠሩት ቤርካኔዎች በ1938 ከተመሰረቱ በኋላ ለካፍ ውድድሮች ፍፃሜ ሲበቁ ይሄኛው የመጀመሪያቸው ነው፡፡
ብርቱካናማዎቹ አዲስ ታሪክ ለማፃፍ ደግሞ የሜዳ ላይ አድቫንቴጅ ይዘው የመልስ ግጥሚያቸውን አሌክሳንድሪያ ላይ በሚገኘው 86 ሺ ተመልካች በሚይዘው የቦርጅ አል አረብ ስታዲየም የ90 ደቂቃ ብቻ ጊዜ ይቀራቸዋል፡፡
ይሄንን የፍፃሜ ግጥሚያ ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ ተሰማ ወየሳ ይመራል፡፡ ረዳቶቻቸው ደግሞ ዛካሊ ሲዎሊ ከደቡብ አፍሪካ እና አልሃጂ ማሊክ ሳምባ ከሴኔጋል እንዲሁም አራተኛ ዳኛው አል- ሳዴቅ አል- ሳልሚይ ከቱኒዚያ ናቸው፡፡
የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊው ቡድን የ1.25 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲሸለም፤ ተሸናፊው የ625 ሺ ዶላር ያገኛል፡፡