ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልትን ወቅታዊ አፈፃፀምና ቀጣይ የአፈፃፀም አቅጣጫ የሚያመላክት ጥናት ልታካሄድ ነዉ፡፡
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ስልት ነባራዊ የአፈፃፀም ደረጃና ቀጣይ ሁኔታዎች የሚያመላክት ጥናት ለማስጀመር ያለመ የምክክርና ጥናቱ መከተል የሚገባው ስልት ላይ ግብዐት ለማሰባሰብ የሚያስችል የምክክር መድረክም ተካሄደ፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የጀመሩት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕ/ር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት “ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልትን ከየትኛውም ሀገር ቀድማ በመቅረፅና በመተግበር አርአያነት ያለው ተግባር መፈፀሟን ገልፀው፤ የስልቱን ውጤት እየፈተሹ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና በገንዘብ ሚኒስቴር የጋራ አስፈፃሚነት የተጠራው የምክክር መድረክ፤ ጥናቱን ለማከናወን የተመረጠውና ፔግሲያስ የተባለው አማካሪ ድርጅት ለጥናቱ መነሻ ይሆናል ብሎ ያከናወነውን መነሻ የጥናት ሀሳብና ጥናቱን ለማከናወን እከተለዋለሁ ባለው የጥናት ስልት ላይ ከባለድርሻዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እንዳገኘነዉ መረጃ፤ በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሣተፋቸው የተገለፀ ሲሆን ጥናቱ ይመልሳቸዋል የተባሉ ሀሳቦችም ቀርበዋል፡፡