የዚምባቡዌ ዶክተሮች የማህበራቸውን መሪ መታገት ለመቃወም የስራ ማቆም አድማ መትተዋል፡፡
ሀራሬ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የህክምና ባለ ሞያዎች ፒተር ከሌለ ስራ የለም የሚል መፈክር ይዘው ነው ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው ሰልፈኞቹ የዚምባቡዌ የሀኪሞች ማህበር መሪ የነበሩት ዶክተር ፒተር ማጎምቤይ ሰሞኑን ታግተው ተወስደዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ዶክተሩ ባለፈው ቅዳሜ እለት በዋትስ አፕ በላኩት መልእክት በማያውቋቸው ሶስት ግለሰቦች ታፍነው መወሰዳቸውን አመላክተው ከዚያን ወዲህ ድምጻቸው አልተሰማም፡፡
የተቃዋሚ መሪው ኔልሰን ቻሚሳ በቲውተር ገፃቸው ላይ በሰፈሩት ፅሁፍ በሰማሁት ነገር ልቤ በሀዘን ተሰብሯል ብለዋል፡፡
ዶክተር ፒተር በቅርብ ሳምንታት ለሀኪሞች የደመወዝ መጠን እንዲሻሻል መንግስት ላይ ጫና ለማሰሳደር ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፎችን ሲያዘጋጁ ነበር ተብሏል፡፡
የዚምባቡዌ መንግስት ቃል አቀባይ ኒክ ማንግዋና የሀኪሞቹን ጥርጣሬ መሰረተ ቢስ ነው መንግስት ዜጎቹን የሚያግትበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም ሲሉ ሁኔታውን አስተባብለዋል፡፡
መንገሻ ዓለሙ