የሕዳሴው ግድብ የብረታብረት ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ::
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የብረታብረት ፍሬም ሥራ 100 ፐርሰንት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የሲቪል ሥራው 87 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ደግሞ 46 በመቶ መጠናቀቁን የሕዳሴው ግድብ ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ።ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ሥጋት በዓለም ላይ ጥላውን ያጠላ ቢሆንም የሕዳሴው ግድብ ሥራ በነበረው ግለት እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 73 በመቶ መድረሱንም አክለዋል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሠራተኞችን በመጠበቅ የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ሥራው ያለ አንዳች እንከን መቀጠል እንዲችል እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ክፍሌ፣ ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘም ችግሮች እንዳይገጥሙ ታቅዶበት እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ግድቡ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ ኃይል ማመንጨት እንዲችል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር ክፍሌ፣ የውሃ ሙሊቱ በሚቀጥለው የክረምት ወራት እንደሚጀምርና እቅዱን በሚገባ ማሳካት በሚቻልበት ቁመና ላይ መሆኑን ተናግረዋል ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።