አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣2012 ኢትዮጰያና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉትን የቴክኒክ ውይይቱን ለመቀጠል ተስማሙ :: ኢትዮጵያና ሱዳን የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የሚያደርጉትን የቴክኒክ ውይይት በሁለቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች አማካኝነት ለመቀጠል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሱዳኑ አቻቸው አብደላ ሀምዶክ ጋር በህዳሴ ግድብ ላይ በኢንተርኔት ውይይት አድርገዋል።የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትርም በውይይቱ ተሳትፈዋል።ውይይቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያልተቋጩ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ እና የተሳሳተ ግንዛቤ የነበረባቸውን ጉዳዮች ያጠራ ንግግር መደረጉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሱዳን በኩል ለተነሱ የአካባቢ ጥበቃ፣ የግድቡ የደኅንነት ሁኔታ እና የመረጃ ልውውጥን ማመቻቸትን ለተመለከቱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህም ባለፈ የግድቡ የግንባታ ደረጃ ያብራሩ ሲሆን ግድቡ ለኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ኢኮኖሚያዊ ትስስር መጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።የግድቡን ግንባታ አስመልክቶ የሚደረገውን የቴክኒክ ውይይት በሁለቱ አገራት የውኃ ሚኒስትሮች አማካኝነት ለመቀጠል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትርጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።