እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1868 መቅደላ ላይ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል በተደረገው ጦርነት የእንግሊዝ ወታደሮች ከዘረፏቸው ቅርሶች መካከል የአጼ ቴዎድሮስ ሹርባ ይገኝበታል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የንጉሱ ጉንጉን ጸጉር ለንደን ውስጥ በናሽናል አርሚ ሙዚየም ተቀምጦ ይገኛል፡፡
ባለፈው ሚያዚያ ወር የአትዮጵያ አምባሳደር ሙዚየሙን ከገጎበኙ በኋላ የይመለስን ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ለጊዜው ለጎብኝዎች እይታ ከተቀመጠበት ቦታ ገለል ተደርጓል ሲል ዘ ጋርዲያን በዘገባው አስነብቧል፡፡
ኢትዮጵያ የልዑል ዓማየሁን አልባሳት ጨምሮ ሌሎች የእጅ ጥበብ ውጤቶች የሆኑና በወቅቱ በእንግሊዝ ወታደሮች የተወሰዱ ቅርሶችን እንዲመለሱላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ብታቀርብም እስካሁን ቁርጥ ያለ መልስ አላገኘችም፡፡
በእንግሊዝ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሁንም በድጋሚ ቅርሶቹ ይመለሱልኝ የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱን ሲያሳውቅ ሙዚየሙ ግን እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል ይላል የዘ ጋርዲያን ዘገባ፡፡