አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣2012
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር ባደረጉት የድጋፍ ስምምነት እና በመንግስት እገዛ ሲካሄድ የነበረው የኮቪድ 19 ቴክኖሎጂ ሶሊዩሽን ቻሌንጅ ዉድድር ተለይተዉ ታዉቀዋል። በአጭር ጊዜ ተተግባሪና መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉት ምርጥ ፕሮጀክቶች ተለይተው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ፍጻሜውን ያገኘውን የውድድር ሂደት በንግግር የከፈቱት የኢኖቬሽን ምርምር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ በችግር ወቅት መፍትሔ ማመንጨት የሚችሉ የፈጠራ ባለሞያዎች እንዳሉን ያመላከተ ነው ብለውታል።
የእውቅና እና የሽልማት ስነ ስርዓት ተሳታፊዎችን ለመደገፍና ለማበረታታት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጎን የተሰለፉትን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተወዳዳሪዎች ላሳዩት ቀና ተሳትፎ አመስግነው ; የቀረቡትን የፈጠራ ውጤቶች ወደ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ለመቀየር እንሰራለንም ብለዋል።
ለአንድ ወር በዘለቀው በዚህ የፈጠራ ባለሙያዎች ውድድር ልየታ ሂደት በጠቅላላው 446 ፕሮጀክቶች ቀርበው ከፍተኛ የቴክኒክ ግምገማውን ያለፉ 30 ፕሮጀክቶች ወደቀጣዩ የግምገማ ሂደት ያለፉ መሆናቸውን የተገለጸ ሲሆን አዋጭነታቸው የተረጋገጡ 12 ፕሮጀክቶች ተመርጠዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ሚኒስቴር ዶ/ር አብርሃም በላይ በመዝጊያ ንግግራቸው፥ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙን ለመከላከል የቀረቡት የፈጠራ ሃሳቦች በሃገር ደረጃ እምቅ የፈጠራ ሃብት እንዳለ የተረዳንበት ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በተጨማሪም የተመረጡትን እነዚህን ፕሮጀክቶች ወደመሬት በማውረድ ህበረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ የተሟላ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡